Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በአውሮፓ ሀገራት ኢትዮጵያን ከወክሉ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያን በአውሮፓ አገራት ከሚወክሉ አምባሳደሮች እና ቆንስላ ጄኔራሎች ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሂደዋል።
 
የቪዲዮ ኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት ለመከላከል እያደረገች ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በማተኮር ተካሂዷል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት ለመግታት እያከናወነች ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ለሚሲዮን መሪዎቹ ገለጻ አድርገዋል።
 
የሚሲዮን መሪዎቹ ከተመደቡበት ሀገር መንግስታት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ወረርሽኙን ለመግታት የሚያስችሉ ትብብሮችን ለማጠናከር እንዲሁም ሀገሮች ወረርሽኙን ለመግታተ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ ተሞክሮ በማስተላለፍ በኩል እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ገዱ መመሪያ ሰጥተዋል።
 
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በሁሉም አካላት ትብብር ለመግታት እንደሚቻል ጽኑ እምነት እንዳላቸው የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ የሚሲዮን መሪዎቹም የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ያሳሰቡት።
 
ዲፕሎማቶች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ በሚኖሩበት ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ተገቢውን መረጃ በማስተላለፍ የማስተባበር ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.