Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በዓመት 58 ሺህ ሰዎች በልብ ህመም ሕይወታቸው ያልፋል – ጥናት

አዲስ አበባበ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 58 ሺህ ሰዎች በልብ ህመም ምክንያት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የጥናት ውጤት አመላክቷል፡፡

በዚህ ጥናት ውጤት መሰረት በየስምንት ደቂቃው የአንድ ሰው ሕይወት ያልፋል ማለት ነው፡፡

የዓለም የበሽታዎች ጫና ጥናት በፈረንጆቹ 2019 የሠራው ጥናት ውጤት እንዳሳየው÷ በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 8 በመቶ ያህሉ ወይም ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች የልብ ህመም አለባቸው፡፡

የልብ ህመም እንደአይነቱ ቢወሰንም በሁሉም ጾታ እና በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ እደሚከሰት ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ ከደም ቧንቧ ጥበት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የልብ ህመም በአብዛኛው በወንዶች ላይ እዲሁም ከጉሮሮ ቁስለት ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የልብ ህመም በብዛት በሴቶች ላይ ይከሰታል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የልብ ሕክምና ክፍል የልብ ስፔሻሊስት ሐኪም እና የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደጁማ ያደታ÷ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ የሚመደበው የልብ ህመም በዓለም የተስፋፋ ቁጥር አንድ ገዳይ በሽታ ነው ይላሉ፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይም ከአኗኗር ሁኔታ ጋር በተያያዘ ስለመጨመራቸው ጠቁመው÷ በጥናቶች እንደተረጋገጠው ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል እስከ 42 በመቶ ያህሉ የልብ ህመምን ያሳያሉ፡፡

ለልብ ህመም አጋላጨ መንስኤዎች

ለልብ ህመም የሚያጋልጡ መንስኤዎች ተፈጥሯዊ እና ከተፈጥሮ ውጭ ተብለው እንደሚለዩ ባለሙያው ይናገራሉ።

በተፈጥሮ ለልብ ህመም አጋላጭ ከሚባሉት ውስጥ በዘረመል የሚተላለፉ ወይም አብሮ የሚወለድ ተጋላጭነት ይጠቀሳል፡፡

ከተወለዱ በኋላ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎች (የጉሮሮ ቁስለት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከሳንባ እና ሌሎችም ጋር የተያያዙ ህመሞች) ከተፈጥሮ ውጭ ያሉ ለልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች መሆናቸውንም ነው ባለሙያው ያብራሩት፡፡

የልብ ህመም ዓይነቶች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በአዳጊ እና ባደጉ ሀገራት መካከል የሚታዩ የልብ ህመም መንስኤዎች እና መከላከያ መንገዶች የተለያዩ መሆናቸውንም ያነሳሉ።

በኢትዮጵያ በባክቴሪያ የጉሮሮ ቁስለት፣ በከፍተኛ ደም ግፊት፣ በደም ኮሌስትሮል፣ ከመጠን ባለፈ ውፍረት፣ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ እዲሁም በደም ቧንቧ ችግሮች የሚከሰት የልብ ህመም መስፋፋቱን አስረድተዋል፡፡

የልብህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ከልብ ህመም ምልክቶች መካከል÷ ከመጠን በላይ ድካም መሰማት (አንዱ የልብ ሥራ እየቀነሰ መሆኑን ያሳያል)፣ በድንገት የሚመጣ ከፊት ለፊት በግራ ደረት በኩል የውጋት ስሜት (ከኮሌስትሮል እና ከአኗኗር ዘዴ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የደም ቧንቧ መዘጋት እና የልብ ህመም ስለሚሆን)፣ እንቅስቃሴ ሳይኖር ከሚያስፈልገው በላይ የልብ ምት መምታት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ምልክቶች (ከእነዚህ ምልክቶች አንዱ) እንደታዩ የልብ ህመም ሊሆን ስለሚችል ቶሎ ወደ ህክምና በመሄድ ማወቅና ጉዳት ሳያደርስ መካከል ይቻላል ይላሉ ባለሙያው፡፡

በዋናነት ለልብ በሽታ አጋላጭ ምክንያቶችን በመገንዘብ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ (ለምሳሌ፡- የደም ግፊት፣ የስኳር እና የኮሌስትሮል መጠንን በየጊዜው በመለካት ብሎም በመከታተል) ለልብ ህመም እንዳንዳረግ ማድረግ ይቻላል ነው የሚሉት፡፡

የልብ ህመም ሕክምና ምንድን ነው?

የልብ ህመም ሕክምና በመድኃኒት፣ በቀዶ ጥገና እና በደም ቧንቧ ስር ሕክምና ይሰጣል፡፡

በኢትዮጵያ በቀዶ ጥገና እና በደም ቧንቧ ስር የሚሰጡት ሕክምናዎች በስፋት ስለሌሉ ሰዎች እራሳቸውን ከህመሙ መጠበቅ እና ሲታመሙም ሳይጸናባቸው ቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ ዶክተር ደጁማ፡፡

በአመጋገብ ረገድ የደም ኮሌስትሮልን ሊጨምሩ የሚችሉ ምግቦችን መቀነስ፣ ጣፋጭ ነገሮችን መቀነስ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሚያመጡ ምግቦችን አለመመገብ፣ የልብ ህመም ያለባቸው ሰዎች ጨው የበዛበት ምግብ አለመመገብን ጨምሮ በአንድ ጊዜ ብዙ መመገብ እንደሌለባቸው የሕክምና ባለሙያው መክረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.