Fana: At a Speed of Life!

የሳንባ ፈንገስ ኢንፌክሽን መንስኤና ምልክቶቹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈንገስ ኢንፌክሽን በሰው ላይ በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠር ይችላል፡፡

የልብና ደረት ውስጥ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ሲሳይ በቀለ እንደገለጹት፥ ሳንባ በፈንገስ ኢንፌክሽን ከሚጠቁ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

እንደ ፎረፎር እና ሌሎች የቆዳ ኢንፌክሽኖች የፈንገስ ኢንፌክሽን መሆናቸውንና በብዛት እንደሚታወቁም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

የሳንባ ፈንገስ ኢንፌክሽን እንደ ቆዳ ኢንፌክሽኖች ብዙም አይታወቁም ያሉት ዶክተር ሲሳይ÷የፈንገስ ኢንፌክሽን በዋናነት በሁለት መንገድ እንደሚከሰት ያስረዳሉ፡፡

የመጀመሪያው አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ የሰውነት የመከላከል አቅም ሲዳከም የሚፈጠር የፈንገስ ኢንፌክሽን አለ ብለዋል፡፡

ሌላው  ስር የሰደደ የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚባለው እንደማንኛውም ኢንፌክሽን የመከላከል አቅም ሳይዳከም የሚፈጠር የፈንገስ ኢንፌክሽን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አብዛኛው ሳንባ ላይ የሚታዩ የፈንገስ ኢንፌክሽኖች የመጀመሪያው አይነት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በዓለም ላይና በእኛ ሀገርም አልፎ አልፎ የሚታየው የሰውነት አቅማችን ሳይዳከም ሳንባን ሊያጠቃ የሚችለው የፈንገስ ኢንፌክሽን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ ፈንገስ ብዙ ጊዜ የሚገኘው በብዛት እርግቦችና የሌሊት ወፍ የሚራቡበት አካባቢ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከእነሱ በሚወጣው አይነ ምድር ላይ ፈንገሱ እንደሚኖር እና ይህ የፈንገስ አይነት አየር ላይ እንደ ብናኝ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ በምንተነፍስበት ሰዓት ወደ አየር ቧንቧ በመግባት ሳንባንና የአየር ቧንቧን ሊያጠቃ ይችላል ነው ያሉት፡፡

ታማሚው ላይም የሚኖረው ምልክት ልክ የአስም አይነት ምልክት መሆኑን፣ ብዙ ጊዜ ሳልና የማፈን ሁኔታም ሊኖር እንደሚችል እንዲሁም መጠነኛ የሆነ ትኩሳት እና አልፎ አልፎ የማላብ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በፊት የቲቢ ሕክምና የወሰዱ ሰዎች እራሳቸውን በደምብ መከታተል ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት፡፡

ምልክቶቹ እየጨመሩ ከሄዱ ለሞት ሊዳርጉ እንደሚችሉ የገለጹት ዶክተር ሲሳይ÷ ምልክቶቹ ሲኖሩ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግና መንስዔውን ማወቅ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

የራስን በሽታ የመከላከል አቅም በመገንባትና በማሳደግ፣ የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ እንዲሁም እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ኢንፌክሽኖችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚቻልም ያስረዳሉ።

ኢንቬሲቭ̎ የሚባለው ከበድ ያለ ኢንፌክሽን መሆኑን ጠቅሰው÷በሆስፒታል ተቋማት መተኛት እና በሚዋጡ የመድሐኒት ሕክምና ሊታከም የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.