Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በሙስና ወንጀል የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በሙስና ወንጀል የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በክልሉ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴ ገለፀ።

የኮሚቴው ሰብሳቢና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ አዩብ አህመድ እንደገለጹት ኮሚቴው አራት የተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎችን በማቋቋም በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ግብረሃይሉ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከህብረተሰቡ ከቀረቡ 38 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች መካከል 16ቱን በመለየት ተገቢው ምርመራ ተደርጎ በስምንት መዝገብ 11 ተካሳሾች ላይ ክስ ተመስርቷል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ከ23 ሺህ ካሬ ሜትር የመንግስት መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ መደረጉን የጠቆሙት ሰብሳቢው ከ12 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ክፍያ መታገዱንም ገልጸዋል።

የሚቀርቡ ጥቆማዎች አነስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ህዝቡ የሚሰጠውን ጥቆማ በማጠናከር የሙስና ወንጀል ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 25 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በቀጣይም እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከሐረሪ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.