Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ለድርቅ የተጋለጡ ዜጎችን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል -የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለድርቅ የተጋለጡ ዜጎችን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ሃይሉ አዱኛ የድርቅ ተጋላጭ ዜጎችን ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ÷ በክልሉ 10 ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 79 ወረዳዎች ለድርቅ ተጋልጠዋል ።

የክልሉ መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ባደረገው እንቅስቃሴ ለ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የምግብ አህል ለድጋፍ ፈላጊዎች መቅረቡምንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ከማሰራጨት ባለፈ በ101 ቦቴዎች ውሃ እየቀረበ መሆኑን እና ለእንስሳት መኖም ከ248 ሺህ በላይ የሣር እስር መቅረቡንም አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 850 ሚሊየን ብር ድጋፍ መገኘቱንም አስታውቀዋል።

በቀጣይም የድርቁ ሁኔታ ከቀጠለ ሁሉም የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ሃይሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.