Fana: At a Speed of Life!

በበለስ-ደብረማርቆስ- ሱሉልታ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበለስ-ደብረ ማርቆስ- ሱሉልታ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ጉዳት መድረሱን የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የጥገና ባለሙያ አቶ አደባባይ አቻው እንደገለፁት ÷በበለስ -ደብረ ማርቆስ – ሱሉልታ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በተፈፀመ ዝርፊያ መስመሩ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

ዝርፊያው የተፈፀመው በተለምዶ አባይ በረሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ የገለፁት አቶ አደባባይ÷ በአንድ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰበትን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ የመጠገን ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ባለሙያው መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተፈፀመው ዝርፊያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ተሸካሚ ምሰሶ አንድ እግር ከነባር ቦታው ሰባት ሜትር ወደ ጎን ቢንሸራተትም የብረት ምሰሶው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበትና ኃይል እንዳይቋረጥ ለማድረግ የመበየድ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የስርቆት ወንጀሉን እንደፈፀሙ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር ውለው ምርመራ እየተካሔደባቸው እንደሚገኝም ነው አቶ አደባባይ የጠቀሱት።

ከስርቆት ወንጀሉ ጋር በተያያዘ ተከሰው ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚተላለፈው የቅጣት ውሳኔ አስተማሪና ወንጀለኞችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያደርግ ባለመሆኑ ለወንጀሉ መበራከት ምክንያት ሊሆን እንደቻለም ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.