Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ለመሰረተ ልማት በተቆፈረ ጉድጓድ በታቆረ ውኃ ሲዋኝ የነበረ ወጣት ሕይወቱ አለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ለመሰረተ ልማት በተቆፈረ ጉድጓድ በታቆረ ውኃ ሲዋኝ የነበረ ወጣት ሕይወቱ ማለፉን የእሳትና ድንገተኛ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ወጣቱ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሚሊኒየም አዳራሽ ጀርባ ለህንጻ ግንባታ በተቆፈረና ውሀ ባቆረ ጉድጓድ ውስጥ ለመዋኘት ገብቶ ህይወቱ አልፏል።

በአዲስ አበባ ተቆፍረው ክፍቱን በሚተው ጉድጓዶች ውስጥ ዋና ለመዋኘትና በሌሎች ምክንያቶች በ2015 ዓ.ም የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል።

በ2014 ዓ.ም በተመሳሳይ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል።

መሰል አደጋዎችን ለመከላከል ጉድጓድ ቆፍረው ለአደጋ ምክንያት የሚሆኑ አካላት በህግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በተቆፈሩና ውሀ ባቆሩ ጉድጓዶች አካባቢ የሚኖር እንቅስቃሴን ማቆምና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የወጣቱን አስከሬን የኮሚሽኑ ዋናተኞች ከአንድ ሰዓት ፍለጋ በኋላ አግኝተው ለፖሊስ ማስረከባቸውንም ነው የተናገሩት።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.