Fana: At a Speed of Life!

ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎች እየሰራች መሆኑን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነትን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ፡፡

ለ125 ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ዘንድሮ ዓመቱን ሙሉ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቶ በትላንትናው እለት በአዲስ አበባ የፈረንሳይ ኤምባሲ የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ፥ የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነትን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ስምምነቱን ትግበራ በማገዝ ፈረንሳይ አጋርነቷን ማሳየቷን ጠቅሰው ፥ በቀጣይም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን የመልሶ ግንባታ ሥራ በማገዝ የፈረንሳይ ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዚዳንት ማክሮን ጋር በቅርቡ በፓሪስ ተገናኝተው፥ የሁለቱ ሀገራት ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።

ሁለቱ መሪዎች ውይይት በተለይም በቀጣይ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶችና የትብብር መስኮች ላይ በማተኮር መምከራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ፈረንሳይ በኢትዮጵያ የሰላም ሂደቱን ትግበራ እያገዘች በኢንቨስትመንት መስክ በስፋት ለመሰማራት ፍላጎት ያላት ስለመሆኑም አምባሳደር ሬሚ ገልጸዋል።

ፈረንሳይ በግብርና፣ በኃይል አቅርቦትና በሎጂስቲክስ ዘርፎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የምታደርግበትን አማራጮች እያየች ትገኛለች ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.