Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መልካቸውን እየቀየሩ የመጡ ሥጋቶችን የሚመክቱ ሥምሪቶች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መልካቸውን እየቀየሩ የመጡና ተለዋዋጭ የሆኑ ሀገራዊ የደኅንነት ሥጋቶችን የሚመክቱ የእቅድ ክለሳዎች በማድረግ ሥምሪት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ተቋሙ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ በመነሳት ያከናወናቸው ተግባራት አጠቃላይ የጸጥታው ሁኔታው እንዲሻሻል አስችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም እንዲጠበቅም አድርጓል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊፈጸሙ የነበሩ የሽብር እንቅስቃሴዎችን፤ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ላይ የታቀዱ ጥቃቶችንና ሀገራዊ ቀውስን ሊያባብሱ የሚችሉ በርካታ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ማክሸፍ መቻሉ እንዲሁም በሥነ ልቦና ጦርነት ረገድ የበላይነት መረጋገጡ፤ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች፤ የተለያዩ ሁነቶች ደኅንነት የተጠበቁ እንዲሆኑ የተከናወኑ ስምሪቶች፤ በአጋርነትና ትብብር መሥኮች የተሠሩ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ ስኬታማ አፈጻጸሞች እንደሆኑ በግምገማው መታየቱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

የተለያዩ ክስተቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአመጽና በግርግር መንግሥታዊ ሥልጣንን የመቆጣጠር ዝንባሌዎች መታየታቸው፤ ሕጋዊ ጥያቄዎችን በኃይል ለማስፈጸም የሚደራጁ ህቡዕ ኃይሎችና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች የሚደቅኗቸው ሀገራዊ የደኅንነት ሥጋቶች መኖራቸው፤ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመፈጸም ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት የማድረግ አዝማሚያዎች በስፋት መንጸባረቃቸው እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትና እሴቶችን ለመሸርሸር የተቀናጁ ዘመቻዎች ሲከናወኑ እንደነበር የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡ እነዚህ ሥጋቶች ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች መክሸፋቸውንም አስታውሷል፡፡

እንደ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ ሀገሪቱ መልካቸውን በቀየሩና ተለዋዋጭ በሆኑ የደኅንነት ሥጋቶች ብትፈተንም ተቋማዊ እቅድን ከወቅታዊና ከተጨባጭ ለውጦች አንጻር በመቃኘት ችግሮችን መሻገር ያስቻለ የተልዕኮ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ እቅዶች ነበራዊ ሁኔታን መነሻ በማድረግ መከለሳቸውና መቃኘታቸው ተቋሙ እንደ ሀገር የተደቀኑ ሥጋቶችን ለመከላከልና ብሔራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዲያበረክት ብሎም ተሰሚነቱ እንዲያድግ አስችሎታል፡፡

በኢትዮጵያ የማያቋርጥ ብጥብጥና የደኅንነት ስጋት በመደቀን ትርፍ ማግኘት የሚሹ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተቀናጅተው እንደሚሠሩ በግምገማው መነሳቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ይህ ሁኔታ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያጋጠመውን ግጭት በሰላም ስምምነት ለመቋጨት የተቻለበትን ስኬት በማጨናገፍ ነገሮችን ወደ ኋላ ለመመለስ በሚደረጉ ጥረቶች እንደሚንጸባረቅ አመልክቷል፡፡ የተቋሙ ስምሪትም ይህን ዝንባሌ ታሳቢ በማድረግ በመከናወኑ ሥጋቶችን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ መቻሉን ገልጿል፡፡

ተቋማዊ ግንባታን ማጎልበት፤ ወቅታዊ የደኅንነት ሥጋቶችን ተገንዝቦ የላቀ አፈጻጸም የሚያስመዘግብ ጥራት ያለው አመራርና ባለሙያ በስፋት የማፍራት ተግባር እንዲሁም ቴክኖሎጂን ለተልዕኮ ከመጠቀም አንጻር የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር በቀጣይ ትኩረት እንደሚሰጣቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ጠቁሟል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.