Fana: At a Speed of Life!

በትራኮማ ምክንያት የሚከሰትን ዐይነ ስውርነት ለመከላከል የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትራኮማ በሽታ ምክንያት የሚከሰትን ዐይነ ስውርነት ለመከላከል እና ለማከም የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በባህርዳር ከተማ ተጀመረ።

በንቅናቄው የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በትራኮማ በሽታ ምክንያት የዐይን ቆብ ፀጉር በመቀልበስ ለዐይነ ስውርነት ተጠቂ ሊሆኑ የሚችሉ ከ100 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች በዘመቻ የዐይን ቆብ ቀዶ ህክምና እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

በመድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን÷ ድህነትና ኋላ ቀርነት የሚያስከትለው ትራኮማ በሽታ ማህበረሰብን የሚጎዳ በመሆኑ በሽታውን ለማከም ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በማህበረሰብ ግንባታ  ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ እና  ህፃናት እና ሴቶችን ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጠቃም አመልክተዋል፡፡

የክልሉን ህዝብ በቀላል ርብርብ ልናክመው እና ከበሽታው ልንከላከለው ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው÷ በአሁኑ ወቅት ከ109 ሺህ በላይ ዜጎች በክልሉ የዐይን ቆብ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡

የማህበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት፣ የባለሙያው እና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ ያለመስራት  ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡

በምንይችል አዘዘው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.