Fana: At a Speed of Life!

4ኛው ቀጣናዊ የፍልሰት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አራተኛው ቀጣናዊ የፍልሰት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባዔው መክፈቻ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ አሰግድ ጌታቸው÷ ኢትዮጵያ ለዜጎች በሀገር ውስጥ የስራ እድልን በመፍጠር ስደትን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እያጋጠሙ ያሉ የሰዎችን ስደት ለመከላከል ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ ጂያን ዣኦ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር ለመደገፍ በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ዛሬ መካሄድ የጀመረው የባለሙያዎች ውይይት ሲሆን÷ ሙያተኞች የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በጉባዔው ማጠቃለያ በሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

በጉባዔው ላይ 11 የምስራቅ አፍሪካ እና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ተወካዮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአራት ቀናት የሚቆየው ጉባዔ የስራ ፈጠራና የሰዎች ፍልሰት በፖሊሲ እና በሌሎች አማራጮች መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.