Fana: At a Speed of Life!

የቀብሪ ደሃር የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀብሪ ደሃር የተገነባው የባለ 132/33 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን የመረቁት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ናቸው።

ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደተናገሩት የኃይል ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በመላው ሀገሪቱ ኤሌክትሪክን ለማስፋፋት ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

በቀብሪ ደሃር የተገነባው የማከፋፈያ ጣቢያና ወደ ጎዴ የተዘረጋው የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

አካባቢውን ከጨለማ ለማውጣት የተሳተፉ ባለሙያዎችን በማመስገን ለአካባቢውና ለክልሉ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው የውሃ፣ የስልክ፣ የጤናና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት መብራት አስፈላጊ በመሆኑ ከሁሉም መሰረተ ልማት ቅድሚያ ትኩረት ይሰጠዋል ነው ያሉት።

በሶማሌ ክልል ለውጥ ከመጣ በኋላ ቀብሪደሀር መብራት በማግኘት ሁለተኛዋ ከተማ እንደሆነች ተናግረዋል።

በቀጣይም እንደ ዋርዴር ያሉት ከተሞች ትኩረት ተሰጥቷቸው ኃይል እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ያልተለመደ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቱ ከታች እስከላይ ባለው መዋቅር ትብብር ስላልተለየው በፍጥነት ሊጠናቀቅ መቻሉን ነው የተናገሩት።

በክልሉ የተገነቡት የኃይል መሰረተ ልማቶች የክልሉን ልማት ለማፋጠንና ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

የፕሮጀክቱ ወጪ የተሸፈነው ከባድያ፣ ከሳውዲ ፈንድ፣ ኦፔክ ፈንድና ከኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ ስልሳ አምስት ሚሊየን ዶላር ወጪ ሲሆን ግንባታውን ያከናወነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ አቅም ቢሮ ነው።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ የጅጅጋ ደገሀቡር 132 ኪቮ ስብስቴሸ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ደገሀቡር ከተማ የ24 የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሆነች ይታወሳል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.