Fana: At a Speed of Life!

በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ3 ሚሊየን በላይ ሔክታር መሬት ተለየ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስድስት ክልሎች 3 ሚሊየን 88 ሺህ 395 ሄክታር ጥልቅ ባልሆነ የከርሰ ምድር ውኃ መስኖ ሊለማ የሚችል መሬት መለየቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

መሬቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተለየ መሆኑንም ኢንስቲትዩቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል።

በዚህም 6 ሚሊየን 176 ሺህ 898 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ እና ጥልቅ ያልሆነ የከርሰ ምድር ውኃ መስኖ ልማት መኖሩን ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2019 እስከ 20222 ድረስ በ30 ሜትር ጥልቀት ለመስኖ አገልግሎት የሚውል የከርሰ ምድር ውሃ ለመለየት ከ234 ሺህ 772 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን ቦታ በካርታ ስራ መሸፈኑም ተጠቁሟል፡፡

የከርሰ ምድር ውሃ ካርታ ስራ ውጤት እንደሚያሳየውም÷ በስድስቱም ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 454 ወረዳዎች 27 ነጥብ 27 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ጥልቀት የሌለው የከርሰ ምድር ውሃ መኖሩ ተለይቷል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና የአየር ንብረት ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ተሾመ እንዳሉት÷ በአጠቃላይ 1 ሺህ 281 የውኃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡

የልየታ ሥራውን መጠናቀቅ ተከትሎም የአቅም ግንባታ፣ የሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ ትውውቅና አቅርቦት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የቴክኖሎጂ መቀበልን ለማሳደግ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች 170 የውሃ ማውጫ ሶላር ፓምፕ፣ ከውሃ ማጠራቀሚያ እና ጠብታ መስኖ ጋር በመልክ በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል ተብሏል፡፡

እንዲሁም በአራት ክልሎች 67 የጉድጓድ ቁፋሮ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም የተመረጠ የጉድጓድ ቁፋሮ ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ስራ በ67 ወረዳዎች ተተግብሯል ነው ያለው።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.