Fana: At a Speed of Life!

በአፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ በ146ኛው የዓለም የፓርላማ ሕብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑካን ቡድን በ146ኛው የዓለም የፓርላማ ሕብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው።
 
የዓለም የፓርላማ ሕብረት ስብሰባ በፈረንጆቹ ከመጋቢት 11 እስከ 15 ቀን 2023 በባህሬን ማናማ የሚካሄድ ሲሆን÷አፈ- ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በስብሰባው ላይ ንግግር አድርገዋል።
 
በንግግራቸውም÷ ኮቪድ -19 በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ያስከተለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አንስተዋል።
 
ሰላምና ደህንነትን ማስፈን ለዴሞክራሲ፣ ለእድገትና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው÷ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የነበራትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
 
በሱዳን፣ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የተደረገውን የሰላም ማስከበር ጥረት፣ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ግንኙነት በሰላም ለመፍታት የተሄደበትን ርቀት እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አጋጥሞ ለነበረው ግጭት ስምምነት መደረሱን አስረድተዋል፡፡
ይህም ለሰላም መሰረት ከመሆኑ ባለፈ በጦርነት ወደ ተጎዱ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ አንዲገባ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
 
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተሞላው የአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነት፣ ግጭትና በቀጠናው በርካታ ችግሮች እንደተደቀኑበትና ይህንንም ለመፍታት ዓለም አቀፍ ጥረትና ትብብር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
 
በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ያጋጠመውን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በምግብ እህል እየመጣ ያለውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግም አመላክተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በውይይትና በንግግር ለመፍታት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ዘላቂ ሰላም እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ጉባዔው በሰላምና ፀጥታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በሚዲያ ጉዳዮች እና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.