Fana: At a Speed of Life!

የሲሚንቶ ስርጭት እና ግብይትን ለመወሰን የወጣው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ ስርጭት እና ግብይትን ለመወሰን የወጣው መመሪያ ቁጥር 940/2015 በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ በሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ሂደት ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም ችግሩ ተቀርፏል የሚል እምነት የለም ብለዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአምራቾች እና አከፋፋዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱም ሚኒስትሩ ለአብዛኛዎቹ አከፋፋዮች ትስስር አለመፈጠሩ፣ የአንዳንድ ፋብሪካዎች ለመመሪያው ተገዢ አለመሆን፣ የደላላዎች ጣልቃ ገብነት፣ ተናቦ ያለመስራት ችግር፣ የአከፋፋዮች እና የቸርቻሪዎች አለመተዋወቅ፣ ያለደረሰኝ የሚካሄድ ግብይት መበራከቱ ለችግሩ አለመቀረፍ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሾቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሲሚንቶ የችርቻሮ ዋጋ በሲሚንቶ አምራቾች ማህበር እንዲወሰን መደረጉን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ዋጋው ከ1 ሺህ 200 ብር እንዳይበልጥ ቢደረግም÷ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ 1 ሺህ 850 ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡

የዚህ መመሪያ ተግባራዊ መደረግ በጎ ጅማሮ ሆኖ ሳላ ነገር ግን አንዳንድ ፋብሪካዎች ለትክክለኛ አከፋፋዮች ያለመስጠት ችግር ይስተዋላል ያሉት በውይይቱ የተሳተፉ አከፋፋዮች ለዚህም እልባት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ አምራቾች በበኩላቸው÷ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አብዛኛዎቹ ሲሚንቶ አምራቾች ከአቅም በታች እያመረቱ በመሆኑ የፍላጎትና የአቅርቦት ያለመመጣጠን ችግር በመከሰቱ ለሁሉም አከፋፋዮች ሲሚንቶ በተፈለገው መጠን ማዳረስ እንዳልተቻለም አስረድተዋል፡፡

በሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ስርዓት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ ስራ እንደሚያስፈግም በመድረኩ መመላከቱን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.