Fana: At a Speed of Life!

የማዳበሪያ ግዥ ላይ 21 ቢሊየን ብር ድጎማ ተደርጓል-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2015/16 የመኸር ወቅት የማዳበሪያ ግዥ ላይ 21 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተያዘው የመኸር ወቅት የማዳበሪያ ግብዓትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ÷ መንግስት ያለውን የትራንስፖርትና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የማዳበሪያ ግብአት ግዥ ላይ 21 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህም በአማካይ በእያንዳንዱ የማዳበሪያ ኩንታል ዋጋ ላይ የ1 ሺህ 566 ብር ድጎማን የሚሸፍን እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይም 370 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ከፌደራል ተቋማት እና የምርጥ ዘር አባዢዎችን በማቀናጀት ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ጉድለቶቹን ለመሙላት የክልል ምርጥ ዘር አባዢዎችን እንጠቀማለን ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

የግብርና ግብአት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ባለፉት ጥቂት አመታት በኮቪድ- 19 እና በሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የግብርና ግብአት ተደራሽነት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር በመፍታት÷ የምርጥ ዘርና የግብርና ግብአቶቹን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለ2015/16 ዓ.ም የመኸር ወቅት ግዥ ተፈጽሞበት ወደብ ላይ ከደረሰው አጠቃላይ ማዳበሪያ ውስጥ 90 በመቶው የክልል ማዕከላዊ መጋዘን መድረሱንም ጠቁመዋል።

ካለፈው ዓመት የቀረውን 2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጨምሮ ለተያዘው ዓመት የመስኖ ፣ የበልግና የመኸር እርሻ ከ 15 ሚሊየን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አመላክተዋል።

በይስማው አደራው እና ዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.