Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ክትባቶችን እንድታመርት ከተለዩ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ክትባት እንዲያመርቱ ከተለዩ ሥድስት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ተገለጸ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ከአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ጋር በመተባበር የክትባት ማምረቻዎችን ለመገንባት ሥድስት የአፍሪካ ሀገራትን ለይቷል፡፡

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ርዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኬንያ እና አልጄሪያ ማምረቻዎቹ ይገነባሉ ተብሏል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጤና ጥበቃ ዳይሬክተር ዶክተር አዴልሄይድ ኦኒያንጎ ÷ ማምረቻዎቹ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መቋቋማቸው ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል ዋስትና ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተቋቋመው የአፍሪካ መድሐኒት ኤጀንሲ አማካኝነት የሀገራትን ወረርሽኝ የመቆጣጠር እና የመቋቋም ዐቅም ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው በአፍሪካ አኅጉር የሚመረቱትን የሕክምና ምርቶች በመቆጣጠር እንዲሻሻሉ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የክትባት ማምረቻዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት በመከላከያ ክትባት እጥረት ሳቢያ የሚደርሰውን የጤና ቀውስ ለመቅረፍና ሀገራቱ በራሳቸው አቅም ቀድመው እንዲዘጋጁ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ባለፉት አመታት በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ በርካታ አዳጊ ሀገራት በክትባት እጥረት መቸገራቸው የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም የዓለም ጤና ድርጅት በሥድስት የአፍሪካ ሀገራት የክትባት ማምረቻ እንዲገነባ ወስኗል።

የማምረቻዎቹ በሥድስቱ ሀገራት መቋቋም አፍሪካ በለጋሽ ሀገራት አቅርቦት ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳትሆን ያስችላል መባሉን አምረፍ ኸልዝ አፍሪካ በመረጃው ጠቁሟል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ቀደም ብላ የክትባት ማምረቻ በማቋቋም የማምረት ሥራ መጀመሯም ተመልክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.