Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ 13 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በመዲናዋ በቱሪዝም ዘርፉ ከውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ 13 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት÷ባለፉት ስድስት ወራት በቱሪዝም ዘርፉ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን የውጭ እና 266 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመቀበል ታቅዶ÷ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን የውጭ እና 224 ሺህ የሃገር ውስጥ ጎብኝዎችን ማስተናገድ ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም ከውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ÷ 13 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል በቴሌ ብር ታክስ እንዲሰበሰብ እና ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አሳውቀው መክፈል እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ከ345 ሺህ በላይ የንግዱ ማህበረሰብ በኦንላይን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ጠቅሰው÷የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን የወረቀት አልባ አገልግሎት በተለያዩ የጤና ተቋማት መተግበሩንም አንስተዋል፡፡

የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በተለይም የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር የማድረጉ ስራ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሥድስት ወራት ወደ ማዕከል ከቀረቡ 230 ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ውስጥ 212 ቅሬታዎች ምላሽ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የነዋሪውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በ5 ሺህ 388 መዝገቦች ላይ ክርክር መደረጉን ገልጸው÷ከእነዚህ ውስጥ በ995 መዝገቦች ላይ ውሳኔ በማሰጠት 877 መዝገቦች ለመንግስትና ለህዝብ ተወስነዋል ብለዋል፡፡

በዚህም ከ386 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ጥቅም ማስከበር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በትምህርት ዘርፉም በሁሉም እርከን የተማሪ ቅበላ ከነበረበት 1 ሚሊየን 34 ሺህ 373 ወደ 1 ሚሊየን 205 ሺህ 630 ለማሳደግ ታቅዶ 1 ሚሊየን 112 ሺህ 745 ተማሪዎችን መቀበል ተችሏል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በ15 የምገባ ማዕከላት በቀን 30 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪችን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡

ከጤና መድህን አባላት ከተሰበሰበ 444 ሚሊየን 259 ሺህ ብር በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ በግማሽ አመቱ ከ227 ሚሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ 246 ሺህ 999 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ እና 37 ሺህ 999 ለሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩንም አንስተዋል በሪፖርታቸው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ በከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረበውን የስድስት ወራት አቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተወያይቶ አፅድቋል፡፡

 

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.