Fana: At a Speed of Life!

በሀረማያ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረማያ ዩኒቨርስቲ በሁለት ሰዓት ልዩነት 384 ናሙና መመርመር የሚችል የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ማዕከል ተመረቀ።

በሀረማያ ዩኒቨርስቲ ሐረር ካምፓስ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያው በተለይ በሐረሪ ክልል እና በአካባቢው በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎችን በመመርመር በውጤቱ በአፋጣኝ የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል እንደሆነ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።

የማዕከሉ ስራ መጀመር በክልሉና በአካባቢው በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎችን በመመርመር በውጤቱ ላይም ተመስርተን በአፋጣኝ ተገቢውን የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

የበሀረማያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ በበኩለካቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ቫይረሱን ለመከላከል በአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰብና ተቋማት በግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የድጋፍ እና የቴክኖሎጂ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው የጤና ባለሞያ አማካይነትም ለአካባቢው ማህበረሰቡ በባለሞያዎች የታገዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጠ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለህሙማን የመተንፈሻ አካልን ሊያግዝ የሚችል መካኒካል ቬንትሌተር እየሰራ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የሳኒታዘርና የፊት መሸፈኛ ጭንብል የማምረት ስራውንም አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የሚገኙ ተማሪዎችን በማሰልጠን ከነገ ጀምሮ በምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች የቤት ለቤት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ለህብረተሰቡ እንደሚሰጡ መናገራቸውን የሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በኮሌጁ የተቋቋመው ላብራቶሪ አስተባባሪ ዶክተር ነጋ አሰፋ በበኩላቸው ላብራቶሪው የተሟላ ግብዓቶች ከተሟሉለት በየሁለት ሰዓት ልዩነት 384 ናሙና መመርመር ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የሚገኘው እና በሁለት ሰዓት ልዩነት 96 ናሙናዎችን መመርመር የሚችለው በሚቀጥለው ሳምንት ስራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.