Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኔን በጦር ጄት መታብኛለች ስትል ሩሲያን ወነጀለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኔን (ድሮን) በጦር ጄት በመምታት በጥቁር ባህር እንዲከሰከስ አድርጋለች ስትል አሜሪካ ወነጀለች፡፡

ዋሺንግተን ኤስ ዩ-27 የተሰኘው የሩሲያ የጦር አውሮፕላን ለአየር ሃይል መረጃ፣ ክትትል እና አሰሳ አግልግሎት ሲውል የነበረውን ኤም ኪው -9 ሰው አልባ አውሮፕላን መቶብኛል ብላለች።

ሩሲያ በበኩሏ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን የተከሰከሰው በረራ ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር መሆኑን ገልጻለች።

ሰው አልባ አውሮፕላኑ ከሩሲያ የጦር ጄቶች ምንም አይነት ጥቃት እንዳልተፈጸመበትም ነው የሩሲያ መከላከያ ያስታወቀው።

ኤም ኪው 9 የተባለው የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ከከፍታ በላይ በመብረሩ እና ከበረራ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር 9፡30 አካባቢ መከስከሱንም አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ሰው አልባ አውሮፕላኑ የሩሲያው ወታደራዊ የአየር ክልል ጥሶ እንደነበርም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከክስተቱ በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭን ስለጉዳዩ ለማነጋገር መጥራቱ ነው የተገለፀው፡፡

አምባሳደር አንቶኖቭ እንደተናገሩትም ሞስኮ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን በጥቁር ባህር አካባቢ ያደረገውን እንቅስቃሴ “እንደ ትንኮሳ ትመለከተዋለች” ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.