Fana: At a Speed of Life!

ተቋማት የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ ለተጨባጭ እድገት ሊሰሩ ይገባል -አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመካከለኛ ዘመን (2016-2018) የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድን ከ5ተኛው ዙር ፕሮግራም በጀት ጋር አጣጥሞ ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ከሶስት ዓመታት በፊት በተዘጋጀውና በመተግበር ላይ ባለው የ10 ዓመት ልማት እቅድ የተመዘገቡ በርካታ ውጤቶች ቢኖሩም በርካታ ተግዳሮቶች ኢኮኖሚ እድገቱን እንደፈተኑት ተመላክቷል፡፡

ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት፣ የዋጋ ንረት፣ የእዳ ጫና፣ ጦርነት እንዲሁም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከፈተኑ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገቶችን ማሳየቱ ነው የተገለጸው፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ÷ መንግስት የተግዳሮቶቹን ጫና ለመቀነስና ለእድገት መመዝገብ ከፍተኛ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል፡፡

የመካከለኛ ዘመን ከ2016-2018 የፐብሊክ ኢንቨስትመንት እቅድ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ከፋይናንስ ጋር ለማቀናጀት ከ5ተኛው ዙር ፕሮግራም በጀት ጋር የማስተሳሰር ስራ የመስራትና ይህንን ስርዓት የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የዝግጅት ሒደትና የሚጠበቁ ውጤቶችን (የልማት ፕሮግራምና ፕሮጀክት ልየታና ቅደም ተከተል ማስያዝ) ላይ አስፈፃሚ ተቋማትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጋራ ግንዛቤ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዕቅዱን በሚጠበቀው ጥራትና መርሐ ግብር እንዲያዘጋጁ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስቴርና በጋራ መካሄዱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተቋማት የመንግስትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ ለተጨባጭ እድገት ሊሰሩ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ አስገንዝበዋል።

ከ5ተኛ ዙር ፕሮግራም በጀት ከእቅዱና ከፋይናንስና ከመንግስት በጀት ጋር አስተሳስሮ መሄድ እና ስርዓትን መገንባትም እንደሚያስፈልግ አጽኦት ሰጥተዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.