Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በግብር ስወራ በየአመቱ ከ40 እስከ 60 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በግብር ስወራ ምክንያት በየአመቱ ከ40 እስከ 60 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ የአፍሪካ የኢኪኖሚ ኮሚሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ሃናን ሞርሲ ተናገሩ።

የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ ልማትና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ሃናን ሞርሲ፥ ይህን ክፍተት መሸፈን ብክነትን በመቀነስ ሃብት ለማሰባሰብ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

አፍሪካ ዓለም ላይ ከፍተኛ በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎች የሚኖሩባት አህጉር መሆኗን የጠቀሱት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፥ በፈረንጆቹ 2022 በአፍሪካ 546 ሚሊየን ሰዎች ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ አመላክተዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም ድህነት ተኮር እና አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመከተል ለሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቀጠናዊ ትስስርና ንግድ ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ በአፍሪካ አሁንም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ትልቁ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀገራት የእርስ በርስ ንግድ ለአፍሪካ አስፈላጊ መሆኑንም አውስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.