Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልልን ለማረጋጋት እና መልሶ ለማቋቋም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች ዛሬ ሁለተኛ ዙር የእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓት ተካሄደ።

በተለያዩ ማስተባበሪያ ቀጣናዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለተወጡ አመራሮች ነው እውቅናው የተሰጠው፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው÷ የትግራይ ህዝብ የገጠመውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮች ለመፍታት አመራሮቹ በከፍተኛ ትጋት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡

በውጤታቸውም የሰላም ስምምነቱ ፍሬ ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርስ፣ ህዝቡ የጦርነትን አስከፊነት ተረድቶ ለስምምነቱ መሳካት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።

የሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲሳለጥ፣ አርሶ አደሩ ወደ መደበኛ ሥራው እንዲመለስ፣ የግብርና ግብአት ወደ ህዝቡ እንዲደርስ፣ የመንግስት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ በአመራሩ ዘንድ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ተብሏል።

አስጊ የሆኑ ቀጣናዎችን በመለየት ሰዎች እንዲረጋጉ በማድረግ፣ ከጦርነት ማግስት ህዝቡን እያማረረ የነበረውን ዘረፋ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር የተቀናጀ ስራ በመስራት መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏ መባሉን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ባለፉት 3 አመታት በሰላም እጦት ምክንያት ሳይከበሩ የቀሩ ህዝባዊ እና ሀይማኖታዊ በአላት በአግባቡ እንዲከበሩ ማድረግ መቻሉም ተመላክቷል፡፡

ተግባራት በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀሙም ከ500 ሺህ በላይ የሚሆን ህዝብን በማማከር፣ የህዝቡን ማህበራዊ መሰረቶች አግኝቶ በማወያየት የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶችን በማወያየት የትግራይ ህዝብን ሊጠቅም የሚችል ስራ ተሰርቷል ነው የተባለው።

በመድረኩ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር÷ የፓርቲውን እና የመንግስትን አደራ ተቀብላችሁ የትግራይ ህዝብ ያጋጠመውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ያደረጋችሁት ጥረት እጅግ የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲም የሰላም ስምምነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመሰል ተግባራት የሚጠበቅበትን ፓርቲያዊ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.