Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰይፍ ሞሀመድ ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የሀገሪቱን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ተሻለ ከፍታ የሚወስድ እና በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ማሳያ አካል ነው ተብሏል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በኩል የአገልገሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እና በተለይም ለአውሮፕላን አብራሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ አገልገሎት አሰጣጥ ለመቀየር የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የትምህርት እና ስልጠና አቅም ግንባታ፣ ከድሮን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የኦፕሬሽን ፍቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችልና ሁለቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን መሰረታዊ አጀንዳዎች ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰይፍ ሞሀመድ÷የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአፍሪካ የሴፊቲ ልህቀት ማእከልን ለመመስረት እና በአጠቃላይ ዘርፉን ለማሳደግ ለያዘው እቅድ ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሚመሰረተው የሴፊቲ ልህቀት ማዕከል የአፍሪካን የአቪዬሽን ደህንነት የበለጠ ለማሳደግ እንደሚረዳ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ እና ከትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዲኤታ ደንጌ ቦሩ ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በመገኘት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.