Fana: At a Speed of Life!

100 ሺህ ለሚጠጉ የሶማሊያ ሥደተኞች እና የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ 101 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል – የዓለም ጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሶማሊያ ተሰደው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሠፈሩ ሥደተኞችን እና ለአካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎች በሰብዓዊ ድጋፍ ለመድረስ 101 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ገንዘቡ ለስደተኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘጠኝ ወራት ድጋፍ ለማድረስ የሚያስፈልግ መሆኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ለሚገኙ ሥደተኞች እና የአካባቢው የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና ድጋፍ ለማቅረብ 5 ነጥብ 86 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡

ከፈረንጆቹ የካቲት 2023 ጀምሮ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሥደተኞች ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሶማሊያ ወደ ኢትጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር አቋርጠው የገቡትት ሥደተኞች አብዛኛዎቹ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ታዳጊዎች እና የቆሰሉ ወይም የታመሙ ሰዎች መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡

ሥደተኞቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ከደረሱ ጀምሮ አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ድርጅቱ አመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት በሶማሌ ክልል በሚገኙ ከ10 በሚልቁ ዞኖች የኮሌራ እና የተለያዩ በክትባት በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚችሉ ወረርሽኝ መቀስቀሱን አስታውሷል።

በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታመማቸውን እና 136 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ተከሥቶ የማያውቅ ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ ዶሎ ዞን የችግሩ ከፍተኛ ተጋላጭ ሆኗልም ነው ያለው፡፡

ድርቁ ሥደተኞቹን ብሎም የአካባቢውን ነዋሪዎች ለከፍተኛ የምግብ ዕጥረት ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ብሎም የእነዚህ አገልግሎቶች በቂ አለመሆንን ተከትሎ ለሚመጣ የተቅማጥ በሽታ ወረርሽኝ እና ኮሌራ መዳረጉንም ነው የገለጸው፡፡

ዶሎ ዞን ዳኖንድ ወረዳ ሥደተኞቹ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተቅማጥ በሽታ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ድርጅቱ ጠቁሟል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.