Fana: At a Speed of Life!

አልማ በ90 ቀናት ከ7 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚስረክብ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከመጋቢት ወር ጀምሮ የሚተገበር የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ንቅናቄ ይፋ አድርጓል፡፡

የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ÷አልማ ባለፉት ሶስት ዓመታት የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክትን በደቡብ ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የማህበሩ ማስተባበሪያ የሙከራ ትግበራ ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡

በቀጣይ ሶስት ወራትም አልማ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በ1 ሺህ 832 ብሎኮች ከሰባት ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስረክብ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም 1 በሊየን 700 ሺህ ብር መመደቡን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ወጭ ቆጣቢና በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶችን ለተጠቃሚ ለማስረከብ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ከዕቅድ ጀምሮ እስከ ፕሮጀክት ትግበራ ማህበረሰብ አሳታፊነቱ ዘላቂ ልማትንና የማህበሩን ገጽታ በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል ያሉት አቶ መላኩ÷ ለ90 ሺህ በላይ ወጣቶችም የስራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ከተመደበው 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ባሻገር ህብረተሰቡ በጉልበት በዕውቀትና በቁሳቁስ በማሳትፍ የማህበሩን የመፈፀም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገርና የህብረተሰቡንተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በላቀ የህዝብ ተሳትፎ፣ በመንግስት አመራር ሰጭነት፣ በአልማ አስተባባሪነት ልማታዊ ትብብር የሚንፀባረቅበት እንደሆነ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት አልማ ባለፉት አመታት ካዳበራቸው አሰራሮችና ምርጥ ተሞክሮዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው÷የአልማ አባላትና የክልሉ ህዝብ እንዲሁም የልማት አጋሮቻችን ለተፈፃሚነቱ ከጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.