Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እግድ ከነገ ጀምሮ ይነሳል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ከነገ ጀምሮ እንደሚነሳ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የባጃጅ አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም÷በባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ከነገ መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚነሳ አስታውቋል፡፡
የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በየትኛውም ርቀት ከ5 ብር በላይ ማስከፈል እንደማይችሉም ነው የተገለጸው፡፡
የሚደራጁበት አግባብ ትክክል አለመሆን፣ የትራፊክ አደጋ መበራከት፣ ህግና መመሪያን ተከትለው አለመስራት እና ደረጃውን የሚመጥን መንጃ ፈቃድ አለመኖር ባጃጆቹ እንዲታገዱ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸው ተነስቷል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት መመሪያ መዘጋጀቱን እና ባጃጆች በመመሪያው መሰረት የሚሰሩበት የስምሪት መስመር እንዲሁም ታሪፍ መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
ስለሆነም ባጃጆቹ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽት 3፡00 ብቻ እንዲሆን መወሰኑን ቢሮው አስገንዝቧል፡፡
ቢሮው ቀደም ሲል የባጃጅ ባለንብረቶችን ለማደራጀት ባካሄደው ምዝገባ በ123 ማኅበራት 9 ሺህ 550 ባለንብረቶች መመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡
በመዲናዋ መደበኛ ትራንስፖርት በማይገኝበት ከ0 ነጥብ 9 እስከ 2 ነጥብ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ በአምስት ብር ታሪፍ አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑም ተገልጿል፡፡
የባጃጅ የስምሪት መስመሮች በከተማዋ ዳርቻዎችና አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በሰፋፊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይቶች እና በተለዩ አንዳንድ የከተማው የውስጥ ለውስጥ አጫጭር መንገዶች ላይ የተወሰነ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ስምሪት ስርዓት ውስጥ መሳተፍ የሚችሉት ኮድ 1 ሰሌዳ ያላቸው ባለሦስት እና ባለአራት እግር በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ተሸከርካሪዎች ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በቢሮው በተለዩ የስምሪት መስመሮች ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጡ እና የመጫን አቅማቸውም 3 ሰው ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዋና መንገድና አደባባይ ላይ የስምሪት መነሻና አገልግሎት አሰጣጥ እንደማይፈቀድ እና የነዳጅ ድጎማ እንደማይደረግም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.