Fana: At a Speed of Life!

ሳዑዲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር እንደምትሠራ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ፋህድ ኦቤዱላህ አል ሃሚዳኒ ገለጹ።

በሳዑዲ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በእንስሳት ሀብት ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር አመላካች ነው ብለዋል።

ያም ሆኖ አሁን ላይ በአገራቱ መካከል ያለው አጋርነት ሁለቱ አገራት ካላቸው የኢንቨስትመንት እና የንግድ አቅም አኳያ እምብዛም አለማደጉን ገልጸው ይህም መሻሻል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፉ ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፣ ትብብሩን ለማጠናከር እንደምትሠራ ነው ያረጋገጡት።

አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ማሳለጥ የሚያስችሉ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ደረጃ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የሳዑዲ ዓረቢያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከግብርና ሰብል ምርት ጀምሮ እስከ ምርትን ለውጪ ንግድ እስከማቅረብ የዘለቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያለው እምቅ አቅም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የሳዑዲ ኢንቨስትመንት ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.