Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ 39 የአልሸባብ አባላት በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 93 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ከ1 ሺህ 118 ጥይቶች ጋር ወደ ኢትዮጲያ በማስገባት እና በመደበቅ የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ 39 የአልሸባብ አባላት በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ የጂጂጋ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ አሊ በሽር ጓሀድ፣ ሆሾኦ አደን ኢብራሂም እና ራህዎ ኢብራሒምን ጨምሮ አጠቃላይ 39 ሲሆኑ፥ በሶስት መዝገብ ተከፋፍሎ ነው ጉዳያቸው የታየው።

ተከሳሾቹ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም መቀመጫውን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ያደረገው የአልሸባብ አለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባል በመሆን በሞቃዲሾ የሽብር ስልጠና በመውሰድ የተለያዩ 93 የጦር መሳሪያዎችን ከ1 ሺህ 118 ጥይቶች ጋር ወደ ኢትዮጵያ ማስገባታቸው እና መደበቃቸው በክሱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ በሶማሌ ክልላዊ በአፍዴር ዞን በኤልከሬ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በክልሉ ልዩ ኃይሎች ላይ ተኩስ በመክፈት የሶስት ልዩ ኃይል አባላቶች ህይወት እንዲያልፍ እና ሌሎች ሶስት የልዩ ኃይል አባላትን በማቁሰል ጥቃት መፈጸማቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሹቹ በቁጥጥር ስር ውለው በታህሳስ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በተናጠልና በቡድን ተሳትፏቸው ተጠቅሶ ተደራራቢ የሽብር ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ተላልፈዋል በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት የሽብር ወንጀል ተደራራቢ ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰነድና የሰው ምስክሮች ቃል እንዲሰማለት ጠይቋል።

ተዘዋዋሪ ችሎቱ በተለያዩ ቀናቶች የዓቃቤ ህግ ምስክሮችን ቃል በማዳመጥ ለፍርድ ቤቱ የቀረቡ የዐቃቤ ህግ የሰነድ ማስረጃዎችን እና የምስክር ቃልን መርምሯል።

ተከሳሾቹ በሽብር አዋጁ መሰረት እንዲከላከሉ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ብይን ተሰጥቷል።

የተከሳሾቹን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ከመጋቢት22 ቀን እስከ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.