Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ በዋናነት እያጋጠሟት ነው ያላቸው አምስት ፈተናዎች

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 7 – 8 ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ በዋናነት እያጋጠሟት ያሉትን አምስት ፈተናዎች ከእነ መፍትሄው አስቀምጧል።

የመጀመሪያው ፈተና

የመጀመሪያው ፈተና ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው ያለው ኮሚቴው፥ “በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም አሉን” ብሏል።

እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም ያለው ኮሚቴው፥ “ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፡፡ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም። የተሻለው የመጀመሪያ መፍትሔ ለዕድሉም ለዕዳውም ተገቢውን ዕውቅና መስጠት፣ ዕድሉን ለመጠቀም፣ ዕዳውን ደግሞ ለማራገፍ ጠንክሮ መሥራት ነው”፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነና የሰከነ አካሄድ አዋጪ መሆኑን የዓለም ታሪክ አሳይቶናል ብሏል።

“ያለፉ ነገሮቻችን ትምህርት እንጂ እሥር ቤት እንዳይሆኑን አድርገን እንሻገራቸው” ሲልም አሳስቧል።

ሁለተኛው ፈተና

ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል ሌለው ፈተና ነው። “ሕዝባችን ባደረገው መራራ ትግል ካገኛቸው መብቶች አንዱ ነጻነት ነው፡፡ አካባቢን የማስተዳደር፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጥ፣ መንግሥትን የመቃወም፣ ሚዲያን የማቋቋምና የመጠቀም፣ እምነትን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት የማምለክ፣ ወዘተ. ነጻነቶችን ሕዝባችን በትግሉ ተጎናጽፏል” ነው ያለው።

“ኃላፊነት የሌለበት የነጻነት ሥርዓት ሥርዓት አልበኛነትን ያመጣል” ያለው መግለጫው፥ በአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሚዲያዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአክቲቪስቶች አካባቢ የሚስተዋለው ነጻነትን የማስተዳደር ችግር፣ በቶሎ ሊገራ የሚገባው መሆኑን ገምግሟል፡፡

 

ሦስተኛው ፈተና

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው በኮሚቴው የተቀመጠው ሶስተኛው ፈተና ነው።

ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ ማንም የበላይና የበታች ሆኖ መኖር አይችልም ያለው ኮሚቴው፥ “አንዳችን ያለ ሌላችን ልንኖር አንችልም፡፡ በመከፋፈልና በመለያየት፣ በግጭትና በጥላቻ ምንም ዓይነት ዕድገትና ብልጽግና አይመዘገብም፡፡ ሰላምና ደኅንነታችንም አይረጋገጥም” ሲል አስገንዝቧል።

የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎች ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁም ጥሪ አቅርቧል።

 

አራተኛው ፈተና

በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ባጋጠሙ ችግሮች የተነሣ በተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በአራተኛ ፈተናነት አንስቷል። ከኑሮ ውድነቱ ጋርም የሥራ አጥ መጠኑ ጨምሯል ብሏል፡፡

ፈተናውን በብቃት ለመሻገር መንግሥት መራር ውሳኔ ሊወስንባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም በማረጋገጥ ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ መንግሥት በችግሩ ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ አካሄዶችን በማረም ምርትን በተገቢ መጠን ለማምረትና ወደ ገበያ ለማድረስ የሚታዩ የአመራርና የአሠራር ችግሮች መፈታት አለባቸው ነው ያለው።

የሕዝቡን ችግር በማባባስ ኪሳቸውን መሙላት በሚፈልጉ ስግብግቦች ላይ አስተማሪ ርምጃ መወሰድ አለበት ብሏል።

 

አምስተኛው ፈተና

ሌብነት ሌላኛው ፈተና ነው። አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት ያሉት ሌብነት የድህነት ወገባችንን እያደቀቀው ነው ብሏል።

“በመንግሥት አካባቢ የሚገኙት ሌቦች መዋቅርና ሥልጣናቸውን ይጠቀማሉ፤ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉት ሌቦች ደግሞ ገንዘባቸውን ለበለጠ ስርቆት ይጠቀማሉ፤ በብሔር ዙሪያ ያሉት ደግሞ ለሌብነታቸው የብሔር ሽፋን ይሰጡታል፡፡

በሚዲያ አካባቢ ያሉት ደግሞ የሌቦቹን ገጽታ ይገነባሉ፤ ሌቦቹ ሲያዙም ብሔራቸውን እየጠቀሱ ሕዝብ የተነካ ያስመስላሉ፡፡ ሁሉም ዓይነት ሌቦች ፍትሐዊነትን ያዛባሉ፤ የሕዝብን ደም ይመጣሉ፤ ስርቆታቸው እንዳይደረስበት ግጭትና ዐመጽ ይቀሰቅሳሉ፡፡

መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ሌቦች ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል ኮሚቴው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.