Fana: At a Speed of Life!

ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች የሚቀርበውን የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰራጨውን አልሚ ምግብ አቅርቦት ማሳደግ እንደሚገባ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በግጭት እና ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች እንዲሁም አቅመ ደካማዎች ይበልጥ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው፡፡

ስለሆነም ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገቢው ጊዜ አስፈላጊውን የአልሚ ምግብ ማቅረብ እንደሚገባ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ዜጎቹ ካለባቸው ጫና እና ዘርፈ ብዙ ችግር አንጻር ለከፋ አደጋ ሊዳረጉ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ 1 ሚሊየን 286 ሺህ 400 ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም አንተዋል፡፡

በሁለተኛው የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ሂደትም በመንግስት እና አጋር አካላት ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ከ5 ሺህ 789 ሜትሪክ ቶን በላይ አልሚ ምግብ መሰራጨቱን አስረድተዋል፡፡

ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም በቀጣይ የአልሚ ምግብ አቅርቦትን ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መንግስታዊ ተቋማት፣ አጋር ካላት እና ታዋቂ ዜጎች እና ዳያስፖራዎችም ችግሩን በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.