Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ብሄራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪ መሀመድ አብዲከር ጋር በተሀድሶ ኮሚሽን ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሄዱ።

ኮሚሽነሩ የተሀድሶ ኮሚሽን የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ በሰላም ስምምነቱ መሰረት ትጥቅ የፈቱ እና በህጋዊ የምዝገባ ስርዓት ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከማህበረሰቡ ጋር መልሶ በመቀላቀል የሀገሪቱ የሰላምና የልማት ሀይል ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ እስካሁን በኮሚሽኑ የተከናወኑ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች እና ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ ስለሚሰሩ የአጋርነትና ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መሀመድ አብዲከር በበኩላቸው በኤይ ኦ ኤም በኩል ኮሚሽኑን በሚመለከት እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ የተሰሩ ስራዎችን ካብራሩ በኋላ በቀጣይም ኮሚሽኑን ለመደገፍ ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

በተያያዘም አምባሳደር ተሾመ ዘጠኝ አባላትን ከያዘው የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ልዑካን ቡድን አባላት ጋር በኮሚሽኑ የእስካሁን የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችና ቀጣይ የአጋርነት የትኩረት መስኮች ላይ መወያታቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.