Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ እንዲያድግ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል – አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ እንዲያድግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና አመራሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥን ጎብኝተዋል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ተመራጭ፣ ግዙፍ እና ግንባር ቀደም ተቋም ነው” ብለዋል።

አየር መንገዱ በበረራ አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ በ77 ዓመታት ታሪኩ በእድገት ግስጋሴ ውስጥ እንደሚገኝና አሁን ላይ ከ13 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ተገልጋዮች የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመላክተዋል።

አየር መንገዱ 141 አውሮፕላኖች ሲኖሩት በ131 አገራት የበረራ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ከእነዚህ ውስጥ 126ቱ አውሮፕላኖች የሕዝብ ማጓጓዣ የተቀሩት 15 ደግሞ የካርጎ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

አየር መንገዱ የለውጥ ስትራቴጂ ግቦችን በማዘጋጀት እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ከ141 ወደ 200፣ የተጓዦችን ቁጥር ደግሞ ከ13 ሚሊየን ወደ 65 ሚሊየን ለማሳደግ እየሰራ ነው ማለታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.