Fana: At a Speed of Life!

የጨረር ሕክምና አስፈላጊነት እና የሚሰጥባቸው ምክንያቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨረር ሕክምና እንደ ደረጃዎቹ ቢለያይም ለየትኛውም የካንሠር ሕክምና ይሰጣል፡፡

በደረጃዎቹ እና ዓይነቶቹ መሰረት የካንሠር ህመም÷ በቀዶ ጥገና፣ በሚዋጥ እና በመርፌ በሚሰጡ መድኃኒቶች እንዲሁም በጨረር እንደሚታከም ባለሙያዎች ይገራሉ፡፡

እስካሁን ድረስ ለካንሠር ሕክምና የሚያገለግለው ጨረር በሁለት መንገዶች እደሚገኝ ይታመናል፡፡

ይኸውም÷ ጨረር (ራዲየሽን) በተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚመረትበት (የሚመነጭበት) መንገዶች መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በሁለቱም ወይ ከሁለቱ በአንዱ መንገድ በሚገኝ ጨረር በካንሠር የተጠቁ ሴሎችን የመግደል ሂደት ነው የጨረር ሕክምና የሚባለው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሠር ሕክምና ክፍል ኃላፊ እና የካንሠር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኤዶም ሰይፈ÷ የጨረር ሕክምና የሚለየው በአብዛኛው ለተወሰነ የሰውነት ክፍል ብቻ (ሎካል ቴራፒ) ስለሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡

በእርግጥ አልፎ አልፎ (በጣም ጥቂት ለሆኑ ኬዞች) ሙሉ የሰውነት ክፍል የጨረር ሕክምና ሊሰጠው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

ዶክተር ኤዶም የጨረር ሕክምና ከቀዶ ሕክምና በኋላ ጨረር ለሚያስፈልጋቸው የህመም ዓይነቶች (ህመሙ እንዳይመለስ ለማድረግ) እንደሚሰጥ ይገልጻሉ፡፡

ለምሳሌ የጡት ካንሠር፣ የጭንቅላት ካንሠር፣ ከአንገት በላይ ለሚወጡ ካንሠሮች፣ የሰገራ መውጫ እና ፊንጢጣ አካባቢ ለሚወጡ ካንሠሮች፣ ጡንቻ እና አጥንት ላይ ለሚወጡ ካንሠሮች እንደየደረጃቸው ከቀዶ ጥገና በኋላ የጨረር ሕክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡

እዲሁም የቀዶ ጥገና ሕክምናውን የተሳካ ለማድረግም ከቀዶ ጥገና በፊት የጨረር ሕክምና የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቅሳሉ፡፡

በተጨማሪም የጨረር ሕክምና ለማስታገሻ፣ ለሕይወት አደገኛ (አስጊ) ሁኔታዎችን ለመከላከልና ለማከም ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል፡፡

ለምሳሌ ሳንባ ላይ በመተንፈሻ አካባቢ የአየር ቧንቧ መዘጋት ቢያጋጥም እሱን ለመቀነስ፣ ከፍተኛ የሆነ ደምና ሌሎች ፈሳሾች ካሉ እነሱን ለማቆም፣ የነርቭ መጎዳት እና (የሰውት አለመታዘዝ ወይም ፓራላይዝ እንዳያጋጥም) እሱን ለመከላል፣ የአጥንት መሳሳት ወይም መሰበር ከተከሰተ ህመሙን ለመቀነስና ለማከም ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

የጨረር ሕክምና በሁለት አይነት ዘዴዎች የሚሰጥ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ሰውነትን ሳይነካ (ልክ እንደ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ) ታካሚው ጨረር በሚሰጥበት ቦታ እንዲተኛ እና እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ከጨረር አመንጭው ጋር ንክኪ ሳይኖር በርቀት (ይህ ሕክምና ቴሌ ቴራፒ እና ኤክስተርናል ቢን ቴራፒ በመባል ይታወቃል) ይሰጣል፡፡

በሌላ በኩል በቅርበት (ይህ ሕክምና ብራኪ ቴራፒ ይባላል) የካንሠር ሕክምና የሚሰጠበት ሁኔታ አለ ይላሉ፡፡

በተፈጥሮ የሚገኙ ጨረር አመንጪ አካላት በህመሙ መገኛ ቦታ በተለያየ መንገድ እንዲካተቱ ይደረግና ጨረር ህክምን የሚሰጥ ሲሆን፥ ይህም በዋናነት ለማህጸን ካንሠር አገልግሎት ይውላል ብለዋል ዶክተር ኤዶም፡፡

እንደ ዶክተር ኤዶም ገለጻ ሁሉም የካንሠር ህመሞች በአንድ ወቅት የጨረር ሕክምና የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ሊገኙ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡

ስሆነም የጨረር ሕክምና እንደሁኔታው እና እንደየደረጃው ቢወሰንም ለየትኛውም የካንሠር ህመም ይሰጣል ይላሉ፡፡

የህመሙ ደረጃ ከፍ እያለ ሲመጣ (በአብዛኛው ከደረጃ 2 በላይ) የጨረር አስፈላጊነትም ይጨምራል ነው ያሉት፡፡

ደረጃ አንድ ላይ ለሚገኙ የካንሠር ህመሞች የጨረር ሕክምና የሚሰጥት ሁኔታ ቢኖርም አስፈላጊነቱ ውስን መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡

ህመሞቹ ከደረጃ አራት በላይ ሲደርሱ (ካንሠሩ ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል ከተሠራጨ) የጨረር ሕክምናው እንደዋና ሕክምና ሳይሆን ለማስታገሻነት እና ለሌሎችም ሁኔታዎች ነው የሚሰጠው ብለዋል፡፡

ባለሙያዋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ ማንኛውም የካንሠር ታማሚ በትንሹ የአምስት ዓመት ክትትል ያስፈልገዋል፡፡

ምክንያቱም እንደየደረጃው ቢለያይም ከ2 እስከ 40 በመቶ የካንሠር ሕመሞች የመመለስ ዕድል ስላላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል)፣ በጅማ እና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች ብቻ ነው የጨረር ሕክምና እየተሰጠ ያለው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.