Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ብቃቱን ይበልጥ በማሳደግ ለቀጣናው ሰላም ጭምር በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮ የመወጣት ብቃቱን ይበልጥ በማሳደግ በአሁን ወቅት ለአካባቢውና ለቀጣናው ሰላም ጭምር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ብርጋዲዬር ጀኔራል ሙዩሶርዳ ናቲጊያ የተመራ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ቡድን የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝቷል፡፡

ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በጉብኝቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአመሰራረት ታሪኩ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአህጉሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃም አንጋፋ የአቪዬሽን ተቋም ነው ብለዋል፡፡

በሰላም ማስከበር ተሳትፎም ግንባር ቀደም ኃይል ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በኩል ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ተባብሮ በመስራት ለሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወታደራዊ አታሼዎቹ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ከየሀገራቱ ወታደራዊ አታሼዎችና ባለሙያዎች ጋር የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተቋሙ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ብርጋዲዬር ጀኔራል ሙዩሶርዳ ናቲጊያ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከመዋቅራዊ አደረጃጀቱ ጀምሮ በሰው ኃይል አቅምና በዘመናዊ የአቪዬሽን ትጥቅ ራሱን በማዘመን በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኮሎኔል ማርኮ ፖዲ በኢትዮጵያ የጣሊያን ወታደራዊ አታሼ እና ኮሎኔል ዢያን ማርክ ኦዘን የፈረንሳይ ወታደራዊ አታሼ÷ በወታደራዊና በሌሎችም መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ያካሄዱት ጉብኝትም በሀገራቱ መካከል በተለይም በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የልምድና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.