Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም ትውልድ በመፅሐፉ ውስጥ ራሱን ያገኛል ብዬ አምናለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም ትውልድ በ “የመደመር ትውልድ” መፅሐፍ ውስጥ ራሱን ያገኛል ብዬ አምናለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፃፈው “የመደመር ትውልድ” መፅሐፍ በዛሬው ዕለት በታላቁ ቤተ መንግስት ተመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

መፅሐፉ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን÷ በሦስት ክፍሎች እና በ10 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡ በአጠቃላይ 274 ገጾች አሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመፅሐፉ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር÷የመፅሐፉን ገቢ በተመለከተ ክልሎች በራሳቸው መንገድ ከሸጡ በኋላ ሙሉ በሙሉ ገቢውን የተለያዩ የትውልድ ግንባታ እና የታሪክ ማቆየት ስራዎች ላይ እንዲያውሏቸው ፈቅደዋል።

በዚሁ መሰረት ገቢው÷ በአማራ ክልል የፋሲል ቤተመንግስትን ለማደስ፣ በኦሮሚያ ክልል የሶፍዑመር ዋሻን ለጎብኚ ምቹ ለማድረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የስፖርት ማዘውተሪያ ኳስሜዳዎችን ለመገንባት፣ በሐረሪ ክልል የጎብኝ መዳረሻዎችን ለማልማት እንደሚውል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ የሚገኘውን የታቦር ተራራ ለማልማት፣ በአፋር ክልል አሳይታ የአውሳ ሱልጣኔት ቤተመንግስትን ለማደስና ታሪክን ለማቆየት፣ በደቡብ ክልል የጥያ ትክል ድንጋይን ለጎብኚ መዳረሻነት ምቹ ለማድረግ ይውላል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በጋምቤላ ክልሎች ቤተ-መፅሐፍት እንዲገነቡ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዳሴ ግድቡን የትውልድ ዐሻራነት የሚዘክር ሙዝየም በገቢው እንዲገነቡ ፈቅደዋል፡፡

መጽሐፉ በመደመር እሳቤ ትውልዱ ሀገር ካለችበት ችግር እንድትወጣ መደረግ ያለበትን ለማመላከት የተፃፈ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ሁሉም ትውልድ በመፅሐፉ ውስጥ ራሱን ያገኛል ብዬ አምናለሁ ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የተበላሸውን ማስተካከል፣ ድሎችን ማስፋት፣ ለትውልድ ቅብብሎሽ መልካም ነገሮችን ማበርከት የመደመር ትውልድ መርሆዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

መፅሐፉ ነገርን በጊዜውና እና በአውድ የመፃፍን እና ታሪክን የማስቀመጥን አስፈላጊነት በመረዳት የተፃፈ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

“የመደመር ትውልድ” በውስጡ፥ “በሕይወታችን በእያንዳንዱ እርምጃችን እየተገለገልን እንደምንኖር መገንዘብ፤ እኛስ ምን ያህል እያገለገልን ነው? ብለን ራሳችንን ለመጠየቅ ይጠቅመናል” የሚሉ ዕሳቤዎች ተነስተውበታል፡፡

“ሌላውን እንደራሱ የሚመለከት፤ ብሔሩንና ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ያስታረቀ፤ የትናንቱን በጎ ነገር ይዞ የትናንቱን ሥህተት የሚያርም፤ ትናንትን ከዛሬና ከነገ ያስማማ፤ በእነዚህ ጉዳዮች የልሂቃንን ስምምነት በማምጣት ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅን የሚያሰፍን ትውልድ ይፈጠርበታል” የሚሉት በመፅሐፉ ከተነሱ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመደመር እሳቤ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ጥቅምት 2012 ዓ.ም “መደመር” እንዲሁም የካቲት 2013 ዓ.ም “የመደመር መንገድ” የተሰኙ ሁለት መፅሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.