Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኦሞ ዞን 25 ሺህ ዜጎች ለጤና ዕክል ተጋልጠዋል – የዞኑ ጤና መምሪያ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን በተከሰተው ድርቅ 25 ሺህ ያህል ወገኖች ለጤና ዕክል መጋለጣቸው የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ከተጋላጮቹ መካከል 10 ሺህ ያህሉ ሕጻናት ሲሆኑ÷ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ነፍሰ-ጡር እና አጥቢ እናቶች ናቸው።

የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አብረሃም አታ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ አሁን ላይ በዞኑ የተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነት በእጥፍ ጨምሯል፡፡

ከዚህ ቀደም ይፈሱ የነበሩ ወንዞች መድረቃቸውና ወንዞቹ ኩሬ ፈጥረው አካባቢውን ለወባ መራቢያ ምቹ ማድረጋቸው ለተላላፊ በሽታው መባባስ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአካባቢው የምግብ እጥረት በመከሰቱ ማኅበረሰቡ በሽታ የመከላከል አቅሙ እየቀነሰ እና ለጤና እክል ተጋላጭነቱ እየጨመረ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ድርቁ በደቡብ ኦሞ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ማሌ፣ በናፀማይ፣ ሰላማጎ እና ያንጋቶም ወረዳዎች ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋ አቶ አብረሃም፡፡

ከወባ በተጨማሪ በልጆች ላይ በብዛት የሚከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝም በአዋቂዎች ላይ እየተከሰተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የተከሰተውን የጤና እክል ለመቆጣጠር ከፌዴራል እና ክልል መንግስት ጋር የክትትል ሥራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

ለተከሰተው የጤና እክል የሚውል የመድሃኒት አቅርቦት ችግር መኖሩን ገልፀው÷ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመራኦል ከድር እና ሰዓዳ ጌታቸው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.