በማላዊ በተከሰተው ከባድ አውሎ ንፋስ የ447 ሰዎች ህይዎት አለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡባዊ ማላዊ በተከሰተው ከባድ አውሎ ንፋስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 447 መድረሱ ተገለፀ፡፡
በትላንትናው እለት በማላዊ ሰዓት አቆጣጠር 7 ሰዓት አካባቢ የደረሰው ከባድ አውሎ ንፋስ(ሳይክሎን) በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደርሷል፡፡
በደቡባዊ ማላዊ በተከሰተው አደጋ የሟቾች ቁጥር 447 የደረሰ ሲሆን ፥ ከ362 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ መፈናቀላቸው ነው የተገለፀው፡፡
የሀገሪቱ የአደጋ አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው ፥ በአደጋው በተጨማሪ 918 ዜጎች ሲቆስሉ 282 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም፡፡
የማላዊ መከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ አባላትና እና የነፍስ አድን ስራተኞች ዜጎችን ለማዳን ርብርብ እያደረጉ ሲሆን ፥ የህክምና ሰራተኞችንና የህክምና ቁሳቁሶችን ጉዳቱ ወደተከሰተበት አካባቢው እያደረሱ ነው ተብሏል፡፡
የማላዊው ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ÷ ለአደጋው ባቀረቡት የድጋፍ ጥሪ መሰረት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎችና ግለሰቦች እንዲሁም የተለያ ሀገራት መንግስታት ምላሽ መስጠታቸውን ገልፀዋል፡፡
በአውሎ ነፋሱ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ፥ ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር በደቡብ ማላዊ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ሲዘጋ ፥ በአካባቢው የሚገኙ 230 ትምህርት ቤቶች ለተፈናቀሉ ሰዎች ማቆያነት እንዲውሉ ይደረጋል ማለቱን ሲጂቲኤን ዘግቧል።