Fana: At a Speed of Life!

ስፖርት ማህበራዊ ግንኙነት የሚጠናከርበት መድረክ ነው- አምባሳደር  መስፍን ቸርነት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ስፖርት ማህበራዊ ግንኙነት የሚጠናከርበት የዲፕሎማሲ መድረክ ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናገሩ፡፡

8ኛው የመላ አማራ ስፖርት ውድድር  በጎንደር ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የባህልና ስፓርት ሚኒስትር  ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉት÷ ስፖርት በትውልድና ሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና አለው።

ማህበራዊ ግንኙነት ለማጠናከር ስፖርት የዲፕሎማሲ መድረክ መሆኑንም የተናገሩት አምባሳደር መስፍን ተተኪ ስፖርተኞችን በመፍጠር ሂደት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ውድድሩ ትልቅ አቅም ሁኗል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል በስፖርት ልማቱ ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ አለው ያሉ ሲሆን ÷ ከስፖርት ልማት ወደ ማልማት የሚል መሪ ሀሳብ በመያዝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  ይሰራል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ ÷ስፖርታዊ ውድድሩ ወንድማማችነትና አብሮነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ልምድ ለመለዋወጥና ባህልን ለማስተዋወቅ የመላው አማራ ጭዋታ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ወጣትና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው÷ የክልሉን ስፖርት ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በስፋት በመስራት ተተኪ ስፖርተኞችን  ለመፍጠር አመራሮች በዘርፉ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

“ስፖርት ለህዝብ አንድነትና ለሀገር ሰላም” በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ 15 ቀናት በሚካሄደው ውድድር 19 ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች  እንዲሁም  በ20 የስፖርት አይነቶች ከ4 ሺህ 500 በላይ ልዑካን እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

በምናለ አየነው

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.