Fana: At a Speed of Life!

የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ በጎ ጅምር ቢኖረውም የበለጠ መዘመንና መስተካከል ይኖርበታል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብር አሰባሰብ ስርዓታችን በጎ ጅምር እና አሰራር ቢኖረውም የበለጠ መዘመንና መስተካከል ይኖርበታል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ የገቢ ንቅናቄ ማስጀመሪያና የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር  ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ባለፉት አመታት በዚህ መስክ አመርቂ የሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከህዝቡ ቁጥር፣ከአለም መዳረሻነት አኳያ ገና ማበብ እና ምቹ ሆና መሰራት እንዳለባት ጠቅሰው÷ይህን ለማድረግ የከተማዋን  የገቢ አቅም ማሳደግና በዚህ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ በእጅጉ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ግብር የመክፈል ስርዓቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ በአንድ በኩል ግብር መክፈልን ግዴታቸው፣ የእርካታ ምንጫቸው አድርገው ሀላፊነታቸውን የሚወጡ እንደ ዛሬዎቹ ልዩ ተሸላሚዎች አኩሪ ዜጎች ያሉባት ከተማም መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ሀላፊነትን ሙሉ በሙሉ ባለመወጣት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እና ጉድለቶች እንደሚታዩም ተናግረዋል አቶ ደመቀ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የግብር አሰባሰብ ስርዓታችን በጎ ጅምር ቢኖረውም የበለጠ መዘመንና መስተካከል ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

በዚህ የግብር አሰባሰብ መስተጋብር ውስጥ አንዳንዶች የመንግስት ተቋማትን ወክለው ባላቸው ሀላፊነት ብርቱዎችን ማበረታታትና ወደ ላቀ ደረጃ እንዲዘልቁ ማድረግ፣ ማስፋት ሲገባ ጉድለት ያለባቸውን እያስተማሩ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግም ሲገባ፣ ያላቸውን ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው በራሳቸው ብይን እየሰጡ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጥ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

አሰራራችንን ማበልጸግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ በገልጽነት የተሞላ የግብር አሰባሰብ ስርዓት እንዲኖር የበለጠ ሀላፊነታችንን መወጣትም ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

በወቅቱ ሀላፊነታቸውን የማይወጡና ያልተሟላ ስራ የሚሰሩትን ደግሞ በማስተማር ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ እውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ከ300 ወደ ብዙ ሺህ ተሸላሚዎች እንዲያድጉ መስራት፣ ማበረታታት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ሰዓት የእያንዳንዱን ጎጆ እያንኳኳ ያለውን የኑሮ ውድነት ተረባርቦ ለመሻገር የገቢ አሰባሰብ ስርዓታችንን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የግብር ግዴታቸውን በአግባቡ ለተወጡ 300 ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷል።

በየሻምበል ምህረት

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.