Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የገጠሟት ፈተናዎች ሀገር በቀል መፍትሄ ላይ እንድታተኩር የሚያድርጉ ናቸው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ የገጠሟት ፈተናዎች ሀገር በቀል መፍትሄ ላይ እንድታተኩር የሚያድርጉ ናቸው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ተናገሩ፡፡

55ኛው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣የኢኮኖሚ ልማት እና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አፍሪካን ያጋጠሟት ፈተናዎች ሀገር በቀል መፍትሄ ላይ እንድታተኩር የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥ አህጉሪቱን ተፅዕኖ ውስጥ የከተቱ ፈተናዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ መሰል ተፅዕኖዎች አፍሪካ በሀገር በቀል መፍትሄዎች ላይ በማተኮር በእድገት ሞዴሏ ላይ እንድታስብበት የማንቂያ ደወል ሊሆኗት ይገባልም ነው ያሉት።

በስብሰባው መክፈቻ የኮሚሽኑ አባል ሀገራት የፋይናንስ፣ እቅድ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች እና ተወካዮች፣የተመድ ተቋማት ኃላፊዎች፣የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

መደበኛ ስብሰባው ለሶስት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፥ ባለሙያዎቹ በአፍሪካ ያለውን ድህነት እና ኢ-ፍትሐዊነት እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ተወያይተው ባቀረቧቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.