Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ በመጋቢ መስመሮች ባጋጠመ ችግር ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ በነበረው ነፋሻማና ዝናባማ የአየር ፀባይ መጋቢ መስመሮች ላይ ብልሽት በማጋጠሙ የተከሰተ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ሊካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው የኃይል መቆራረጥ በዋናነት በአራት መሰረታዊ ምክንያቶች እንደሆነም አስረድተዋል።

የወቅቱ አየር ሁኔታ፣ ከተማ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እየተከናወነ ያለ የጥገና ሥራና በመሰረተ-ልማት ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች መሆኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በጣለው ዝናብ ምክንያትም ካሉት 137 መጋቢ መስመሮች ውስጥ 50 በሚሆኑት ላይ ብልሽት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የኃይል አቅርቦቱ ወደነበረበት እንዲመለስ እና አስተማማኝ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ላጋጠመው ችግር ለተገልጋዮች ይቅርታ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቃዱ ዘለቀ በበኩላቸው÷ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከወትሮው በተለየ የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ማጋጠሙን ጠቅሰው በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የነበረው የፈረቃ ሥርጭት ላይ መዛባት መፈጠሩንም ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ በቀን እስከ 725ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያመረተ እንደሚገኝና አሁንም የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.