Fana: At a Speed of Life!

በዝናብ ወቅት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የበልግ ወቅት ዝናብን ተከትሎ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጠየቀ፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው ክፍት በተተው ጉድጓዶች፣ በውሃ መውረጃ ቱቦዎች፣ በፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ወንዞች ደረቅ ቆሻሻዎችን መጣል የጎርፍ አደጋ እንዲከሰትና እንዲባባስ ስለሚያደርግ ሕብረተሰቡ አካባቢውን በማፅዳት አደጋን እንዲከላከል ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

የኤሌክትሪክ መስመሮችን ተጠግተው የሚገኙ ዛፎች፣ የረገቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችና የዘመሙ ምሶሶዎች ዝናብ በሚጥልበት ወቅት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ የሚመለከታቸው አካላት የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቀዋል፡፡

እንዲሁም ሕብረተሰቡ በቤት (በሥራ ቦታ) የኤሌክትሪክ መገልገያ መሳሪያዎች ከኃይል ማከፋፈያ መቋረጣቸውን ሳያረጋግጡ ትተው መውጣት እንደሌለባቸው ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡

በቅዝቃዜ ወቅት ሕብረተሰቡ ከሰልን ሲጠቀም በርና መስኮት በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ እና ከሰሉን በውሃ በማጥፋት ሊደርስ የሚችልን አደጋ መከላከል ይገባዋል መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.