Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ዓመት 20 ድሮኖችን የሠራው ኢትዮጵያዊ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አማኑኤል ባልቻ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና መምህር ነው፡፡

በአንድ ዓመት የተለያየ መጠን እና አገልግሎት ያላቸውን “ፊክስድ ዊንግ” እና “መልቲ ኮፕተር (ሮተርስ)” በሚሉ ሣይንሳዊ ምድቦች የሚታዩ 20 ድሮኖች ሠርቷል፡፡

ድሮኖቹ የተሠሩት በዩኒቨርሰቲው ቤተ ሙከራ ከሚገኙ ቁሶች ነው፡፡

“ኳድ ኮፕተር፣ ኦክቶ ኳድ ኮፕተር እና ዋይ-6 (Y-6) መልቲ ኮፕተር” የተሰኙ የተለያየ መጠን ያላቸው ድሮኖችን በአንድ ወር ሠርቷል የፈጠራ ባለሙያው፡፡

ድሮኖቹን በሪሞት እና በኮምፒውተር ‘ሚሽን’ በመስጠት ማብረር ይቻላል ይላል፡፡

ከአንድ ማዕከል (ማዘዣ ጣቢያ) ሲታዘዙ ከ1 እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንዲበሩ የሚያስችል ‘ሪሞት’ እንዳለውም ነው የገለጸው፡፡

የፈጠራ ሥራዎቹም ÷ ወረቀት ለመበተን፣ ኬሚካል ለመርጨት፣ ለድምጽ ማስታወቂያዎች፣ ለቀረጻ፣ ለእሳት ማጥፊያ እና ለሌሎችም አገልግሎቶች እንደሚውሉ አብራርቷል፡፡

በአማካይ ከ300 ሚሊ ሊትር እስከ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም የመሸከም አቅም እንዳላቸውም ያስረዳል፡፡

የፈጠራ ባለሙያው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው ÷ አሁን የተሠሩት ድሮኖች በመሸከም አቅማቸው እና በሚሸፍኑት ርቀት “በቂ የሚባሉ አይደሉም”፡፡

ይህ ድሮኖችን መስራት እንደምንችል ማሳያ ነው እንጅ መሻሻል እንዳለባቸው አምናለሁ ይላል፡፡

አሻሽሎ ለመሥራትም እንደ የሞተር ታይፕ፣ የባትሪ ታይፕ፣ ሃይ ቮልቴጅ ሊፖ ባትሪ፣ ሎንግ ሬንጅ ሪሞት (ትራንስሚተር)፣ ኤፍ ፒ ቪ ካሜራዎች ያሉ እና ሌሎችም ለድሮን ሥራ አስፈላጊ ቁሶች በሀገር ውስጥ አለመገኘታቸው ዕንቅፋት እንደሆነበት አንስቷል፡፡

በመንግሥት በኩል ለድሮን ሥራ አስፈላጊ ቁሶች ወደ ሀገር ውስጥ ቢገቡ ÷ ለወታደራዊ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለእሳት አደጋ ማጥፊያ፣ ለካርታ፣ ለቀረጻ አገልግሎት የሚውሉ ከፍተኛ ክብደት የሚሸከሙ እና ረዥም ርቀት የሚጓዙ ድሮኖችን የመሥራት አቅሙ አለኝ ብሏል፡፡

የግብርና ድሮኑን በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

“እንደዚህ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ለምተው ሀገርን መጥቀም እንዲችሉ ዩኒቨርሲቲው ምን እገዛ እያደረገ ነው” ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ÷ ዩኒቨርሲቲውን በቴክኖሎጂና በፈጠራ ሥራዎች የልኅቀት ማዕከል ለማድረግ የፈጠራ ተሰጥዖ ላላቸው ወጣቶች ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም የፈጠራ ሥራቸውን የሚሠሩበት የሣይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ (STEM) ማዕከል መዘጋጀቱን፣ የቁሶች እና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡

ሥራቸውን በስኬት በመሥራት ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዩኒቨርሲቲው እየሠራ ነው ይላሉ፡፡

ፈጠራውን ወደ መደበኛ አገልግሎት ለማስገባት አስፈላጊ ግብዓቶችን እያቀረብን ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ በዘርፉ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ÷ የትራፊክ አደጋን የሚከላከል የአሽከርካሪ መነጽር፣ የእሳት አደጋን የሚከላከል ሴንሰር፣ አደጋ ሊደርስ ሲል ቀድሞ የሚያነቃ ኮምፒውተር (ስልክ) ላይ የሚጫን የደኅንነት ማንቂያ፣ የእንጨት መሠንጠቂያ ማሽን፣ ከዲሲ ወደ ኤሲ በመቀየር 24 ሰዓት የሚሠራ ጄኔሬተር፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (ስልክ በመደወል) መብራት ማብራት (ማጥፋት) የሚችሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎች በወጣቶች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.