Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ህወሓትን ከሽብርተኛ ድርጅት ዝርዝር ሰረዘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኛ መዝገብ ለማንሳት በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔውን አፅድቋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፥ ህወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲወጣ የተደረገበትን ምክንያት ሲያነሱ፥ “ግጭቶች ሌላ ግጭቶችን እየወለዱ እንዳይቀጥሉ ከጦርነት አዙሪት ለመውጣት፣ የጥላቻና የክፋት ዘርን ለማስቀረትና የፖለቲካ ችግሮችን ለመቅረፍ የህወሓት ከአሸባሪነት ዝርዝር መውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ህወሓት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ያደረጉትን ተግባራት እያሻሻለ መምጣቱን እንደአንድ ምክንያት አንስተዋል፡፡

በሰላም ስምምነቱ የህወሓት ኢ-ህገመንገስታዊ አካሄዶች እንዲቀለበሱ መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ ፥ ባለፉት አራት ወራት ከጦርነት ድባብ እንድንወጣና ህዝቡም እፎይታ እንዲያገኝ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

ይህ ፍሬ እንዲያፈራና አካታች ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ህወሓትን ከአሸባሪነት ማውጣት ማስፈለጉን አስረድትዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፍሬ እያፈራ መሆኑንና በዘላቂነት ይሄን ለማጽናት ሃሳቡ መቅረቡንም ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላትም “ጊዜው አሁን ነው ወይ? ግጭቶችን ለማስቆምስ ምን ታስቧል? የህወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገታስ ምን ተስቧል? የህዝብ ጥያቄስ ነው ወይ?” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

ለጥያቄዎቹም የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸው፥ ህወሓት በአሸባሪነት የተፈረጀበት ምክንያት ውጊያ በመክፈቱ፣ ለፌዴራል መንግስት እውቅና በመንፈጉ፣ ያልተፈቀደ ምርጫ በማካሄዱ እና ሌሎች ሁኔታዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የሚነሳበት ምክንያት ደግሞ ፓርቲው ህገ መንግስቱን ለማክበር በመስማማቱ፣ ትጥቅ ለመፍታት አበረታች ጅምር እና ሂደቶች በማሳየቱ እና ህጋዊ እና አካታች መዋቅር በማደራጀት ላይ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የህግ ተጠያቂነት ያላቸውን ጉዳዮች በተመለከተም በተጀመረው የሽግግር ፍትህ ሂደት ጉዳያቸው ይታያል ነው ያሉት ዶክተር ጌዲዮን ፡፡

በክልሉ አገልግሎቶችን ለመመለስ፣ በጀት ለማዳረስ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ያስፈልጋሉም ብለዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በዘላቂነት እንዲተገበር ግን አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ፥ እነዚህንም ቀሪ ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ እና አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ህወሓትን ከአሸባሪነት ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ለሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የሀገሪቱን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ባከበረና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት በፌደራል መንግስት እና በህወሓት በኩል ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገለግሎቶች እንዲጀመሩ እና የሰብዓዊ እርዳታ በተሳለጠ መልኩ እንዲቀርብ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።

ህወሓትም ታጣቂዎቹን ወደ ካምፕ በመሰብሰብ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማስረከቡም አይዘነጋም።

በዚህ የሰላም ስምምነት መሰረትም ነው ድርጅቱ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲነሳ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ያፀደቀው።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.