Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ የአካባቢ ጥበቃ  ስራዎች ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እተተገበሩ ያሉ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልዛቤት ማሩማ አስታወቁ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ልዑካን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልዛቤት ማሩማ፥ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የምታከናውናቸውን ተግባራት የተባበሩት መንግስታት እውቅና የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል እና በአካባቢ ጥበቃ ስራ ረገድ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ያደነቁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፥ ይህም ለሌሎች ሃገራት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እጅግ ውጤታማና አካባቢን ለመኖሪያነት ምቹ እንዲሆን የሚያደርግ ተግባር መሆኑን እና በዚህም ኢትዮጵያ በዘርፉ የአፍሪካ መሪ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ ተግበራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.