Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለህንጻ ግንባታ የተቆፈረ አፈር ተንዶ የ2 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ለህንጻ ግንባታ መሰረት የተቆፈረ አፈር ተንዶ የሁለት ሰራተኞች ሕይወት አለፈ፡፡

አደጋው በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8:59 ላይ ልዩ ቦታው መነን ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መከሰቱን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ለህንጻ ግንባታ ስራ የተቆፈረው አፈር ተንዶ በስራ ላይ የነበሩ ሁለት ሰራተኞች ሕይወታቸው ማለፉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እንዲሁም ከጸጥታ አካላትጋር በመተባበር የሟቶችን አስከሬን ማውጣት መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመዲናዋ በግንባታ ስራዎች ላይ መሰል ተደጋጋሚ አደጋዎች እየተከሰቱ በመሆኑ አሰሪዎችና ሰራተኞች አስፈላጊውን የደህንነት መስፈርት ጠብቀው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተከሰተው አደጋ የተሰማውን ሀዘን ገልፆ÷ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.