Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የአፈፃፀም ደንብ ህዝቡ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የአፈፃፀም ደንብ ህዝቡ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ተጠየቀ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን በበላይነት የሚመራው የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሚቴው አባላት ሚኒስትሮችና ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ዛሬ መወያየታቸው ይታወሳል።

ከውይይቱ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሲክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ወጥቶ ይፋ የተደረገ ቢሆንም ደንቡን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ላይ ግን አሁንም ክፍተቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሃይማኖት ተቋማትና የገበያ ስፍራዎችም አንዳንዶች የወጣውን ደንብ የመተላለፍ ዝንባሌዎችን እያሳዩ በመሆኑና ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር የማስተማር ስራው ቀጣይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም አስገዳጅና ክልከላ የተደረገባቸው ድንጋጌዎች እንዲተገበሩ ይሰራል ብለዋል።

ለአፈፃፀሙ ህዝቡ በማክበርና በማስከበር ሂደት የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ሂደት ደንቡን የሚተላለፉ አካላት ሲያጋጥሙም የፀጥታ መዋቅሩ አስፈላጊና ተመጣጣኝ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተመራ እና በኮሚቴው አቅጣጫ እየተቀመጠ የአስተምሮና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት በኮሚቴው በማዕከላዊነት ይቀጥላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.