Fana: At a Speed of Life!

ከአንድ ግብር ከፋይ 70 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለው የገቢዎች ባለሙያ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ ሰነድ አቅርበሻል በሚል ከአንድ ግብር ከፋይ 70 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለው የገቢዎች ባለሙያ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በቂርቆስ ክ/ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርጫፍ ጽ/ቤት የአወሳሰን ባለሙያ የሆነው ግለሰብ÷ የቅርጫፍ ጽ/ቤቱ ግብር ከፋይ የሆኑትን ግለሰብ ያቀረብሽው ደረሰኝ የተበላሸ ነው በማለት ጉዳዩን ለማስተካከል ከግብር ከፋይዋ 100 ሺህ ብር ጉቦ መጠየቁ ተመላክቷል፡፡

የግል ተበዳይ ያቀረቧቸው ሰነዶች ትክክለኛ እንደሆኑ ለማስረዳት ቢሞክሩም ባለሙያው ሳይቀበላቸው መቅረቱን እና በቢሮ ስልክ ደጋግሞ በመደወል የግል ተበዳይን በማስጨነቅ እና በህግ እንደሚጠየቁ በማስፈራራት 70ሺህ ብር ጉቦ ለመቀበል ማስማማቱ ተጠቁሟል፡፡

የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለተቋሙ ኃላፊዎች ማሳወቃቸውን ተከትሎ በቂርቆስ ክ/ ከተማ የደንበል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ክትትል ባለሙያው 22 አካባቢ ገንዘቡን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የዚህ ወንጀል ተባባሪ የሆነው በተቋሙ የጥቆማ አቀባበል ባለሙያ ከፍተኛ ኦፊሰር ሰራተኛ ደግሞ በተመሳሳይ ቀን በጉቦ የተገኘውን ገንዘብ ሲቀበል መገናኛ አካባቢ እንደተያዘ ተገልጿል፡፡

ማህበረሰቡ መሰል ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ አካላት አጋልጦ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.