Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በጅምር የህንጻ ግንባታ ስራ ላይ በተሰማሩ 217 ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅምር የህንጻ ግንባታ ስራ ላይ በተሰማሩ 217 ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

በከተማዋ ተተለያዩ ቦታዎች በግንባታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የተወሰኑ አካላት የግንባታ ሰራተኞችን እንዲሁም ማህበረሰቡን ለጉዳትና ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ግንባታ ሲያከናውኑ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተዘዋውሮ መመልከት ችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ አሸዋና ድንጋይ በእግረኛ መንገዶች ላይ በመድፋት መንገድ በመዝጋት ህገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ በጅምር ግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት መኖራቸውንም ነው የታዘበው።

በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ የመስክ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ የግንባታ ስራ በሚከናወንባቸው አካባቢ የሚኖሩ ግለሰቦች ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ዘርፍ ዳይሬክተር ከማል ጀማል፥ ቀደም ሲል የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ተከትሎ የመስክ ክትትል በማድረግ ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።

አሁን ግን የሰው ኃይል ክፍተቶችን በመቅረፍ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በተሰራ የቁጥጥር ስራም በያዝነው ግማሽ ዓመት በጅምር የህንጻ ግንባታ ስራ ላይ ተሰማርተው የሰራተኞቻቸውን የደህንነት ግብዓቶች እና ሌሎች መስፈርቶችን ሳያሟሉ የተገኙ 217 ፕሮጀክቶች ላይ ከአስተዳደራዊ እስከ ፍቃድ ማገድ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል 450 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የተቀጡ እንደሚገኙበት ጠቅሰው፥ ሌሎች ሶስት ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ የግንባታ ፍቃድ የማገድ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል።

በተያያዘ ከትናንት በስቲያ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በሚገኝ ጅምር ግንባታ ስራ ላይ በጥንቃቄ ጉድለት የተከመረ አፈር ተደርምሶ የሁለት ሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ የህንጻው ባለቤት፣ ተቋራጩ እና አማካሪው ጭምር ፍቃዳቸው መታገዱንም ነው የገለጹት።

ተጨማሪ የወንጀልና የተጠያቂነት ማጣራት እንዲደረግ ጉዳዩ ለፍትህ ቢሮ መላኩን በመጥቀስም፥ በቀጣይ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድመው የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል የግንባታ ተረፈ ምርቶች አሸዋና ድንጋይ ማታ ማታ በእግረኛ መንገዶች ላይ በመድፋት መንገድ በመዝጋት ደንብ የሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈሪ ደንብ በመተላለፍ ህገወጥ ተግባር የፈጸሙ 653 የህንጻ አስገንቢ አካላት ላይ ከአስተዳደራዊ እስከ ገንዘብ ቅጣት የደረሰ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.